Addis Ababa ITDB - Innovation...

image description
- In Technology Trends    0

Addis Ababa ITDB - Innovation and Technology Development Bureau

ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

ወጣቶች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ክህሎታቸውን ለአፍሪካውያን ዕድገት 

ወጣቶች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ክህሎታቸውን ለአፍሪካውያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሳለጥ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከ48 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች የተሳተፉበት 2ኛው አህጉራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር የማጠቃለያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በውድድሩም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች 3ኛ ደረጃን በመያዝ 4 ሺህ ዶላር የተሸለሙ ሲሆን፤ የቱኒዚያ ወጣቶች በውድድሩ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን በመያዝ 16 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸልመዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተወካያቸው የአስተዳደሩ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ዝግጅቱ የትጋትና የፈጠራ ውጤት የታየበት ትልቅ የቴክኖሎጂ እምርታ መሆኑን ገልጸዋል።

የአህጉሪቱ ታዳጊዎች በአዲስ አበባ ሲያካሂዱት የቆዩት የፈጠራ ውድድር የዜጎችን ህይወት የሚቀይር የአፍሪካ ወጣቶች አስደናቂ ችሎታና አስተዋይነት የታየበት አበረታች ጅማሮ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው የፈጠራ ተሰጥኦ ባለቤት ታዳጊዎችም የኢትዮጵያና የአፍሪካ ዕድገት መሰረት ናቸው ብለዋል።

በቴክኖሎጂና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ክህሎት የተካኑ ወጣቶች የከተሞችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተሻለ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የፈጠራ መፍትሄዎችን ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሳለጥ ገንቢ ሚና መጫወት በሚያስችል መልኩ ማፍለቅና መጠቀም እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፣ ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ ለዲጂታል ፋይናንስ፣ ኢ-ኮሜርስና አይ.ሲ.ቲ አገልግሎትን ለማሳለጥ አይተኬ ሚና አለው ብለዋል።

ዝግጅቱም አፍሪካውያን ወጣቶች ከሚያደርጉት የፈጠራ ውድድር ባሻገር የባህል፣ ልምድና ተሞክሮ እንዲለዋወጡ ለማስቻል ገንቢ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የአብርሖት ቤተ-መጽሐፍት እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ስራ አስኪያጅ ውባየሁ ማሞ፤ ውድድሩ የአፍሪካ ወጣቶች የፈጠራ ብቃትና ችሎታ የታየበት ነው ብለዋል።

ውድድሩ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መስክ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአፍሪካውያን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ እንደሚገኝ ማሳየቱን ገልጸዋል።

ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በተጀመረው የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ውድድር በአብርሖት ቤተ-መጽሐፍት፣ በአፍሪካ ሲልከን ቫሊና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትብብር "አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለበጎ ተጽዕኖ" በሚል መሪ ሃሳብ ከ48 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 4ሺህ 928 ወጣቶች ሲሳተፉ መቆየታቸው መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments